ሀዋሳ፡ 15/2014 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለጋራ ሠላማችን ዘብ በመቆም የተረጋጋችና ብልጽግናዋ የተረጋገጠላት ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባ የኮቾሬ ወረዳ ሠላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ገልጿል።
የኮቾሬ ወረዳ ሠላምና ጸጥታ ጽ/ቤት "ሠላም ለሁሉም" በሚል መሪ ቃል የ2014 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የጸጥታ ጉባዔ አካሂዷል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ማሩ መድረኩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት አንደተናገሩት፤ ሠላም ለሰብዓዊና ሰብአዊ ላልሆኑ ፍጥረታት ሁሉ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሠላም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
ሕገ ወጥነትንና ወንጀልን በመከላከሉ ረገድ የጸጥታ አስከባሪዎች ድርሻቸው ከፍተኛ ቢሆንም ያለሕዝብ ተሳትፎ ውጤታማ ሊሆኑ ስለማይችሉ ሕብረተሰቡ የራሱን አከባቢ ደህንነት ከመጠበቅ ጀምሮ ሀገሪቷን ለማረጋጋት በሚደረገው እንቅስቃሴ አሻራውን ማሳረፍ ይኖርበታል ሲሉም አክለዋል።
አቶ ዘለቀ ጅግሶ የኮቾሬ ወረዳ ሠላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ በወረዳው ከአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ጋር የተያያዙ ትንኮሳዎች ስጋት እንደሚስተዋሉ ጠቁመው በመንግሥትና በሕዝቡ የተባበረ ክንድ በቁጥጥር ሥር ለማዋል መቻሉንም አንስተዋል።
የሕግ የበላይነት ያልተረጋገጠበት ሀገር ለዜጎቹ ምቹ ካለመሆኑም በላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ለማራመድ አይቻልም ያሉት አቶ ዘለቀ በተለይም የጸጥታ አስከባሪዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነትና ሕዝባዊ አደራን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በበኩላቸው ሥርዓት አልበኝነት ለሠላም መደፍረስ ዋነኛው መንስኤ መሆኑን በመጠቆም መንግሥት በሕገ ወጦች ላይ እርምጃ በመውሰድ በሀገሪቱና በሕዝቡ ላይ የሚቃጣውን አደጋ መመከት ይኖርበታል ብለዋል።
በመድረኩ የኮቾሬ ወረዳ ፍትህ አካላት፣ ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ ፖሊሶች፣ የሚሊሺያ አባላትና ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል።
ዘጋቢ፡ እስራኤል ብርሃኑ - ከፍሰሃገነት ጣቢያችን