ለኢንቨስትመንት መሬት ተረክበው ወደ ስራ ባልገቡ ፕሮጀክቶች ላይ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 04/2014 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለኢንቨስትመንት መሬት ተረክበው ወደ ስራ ባልገቡ ፕሮጀክቶች ላይ የእርምት እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ፡፡
በወረዳው እየተሰሩ ያሉ የኢንቨስትመንትና ሌሎችም የመሰረተ ልማት ስራዎች ያሉበት ደረጃ የተመለከተ የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ለኢንስቨስትመንት ምቹና ተመራጭ በመሆኑ በርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኢንቨስትመንት ልማት ስራዎች ላይ እየተሰማሩ ይገኛሉ፡፡
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ በዚህ ወቅት እንደገለፁት በወረዳው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በመጎብኘት ያሉባቸውን ጥንካሬዎችና ውስንነቶችን በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይገባል፡፡
በወረዳው የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ውጤታማ በማድረግ የህብረተሰቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ዋና አስተዳዳው ገልፀዋል፡፡
የወረዳው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በማሳደግና በማስፋት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ከመቻሉም ባሻገር በበጀት ዓመቱ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ከዘርፉ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡
በወረዳው ለኢንቨስትመንት መሬት ተረክበው ወደ ስራ ባልገቡ ፕሮጀክቶች ላይ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የ3 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውል በመሰረዝ 80 ሄክታር መሬት ማስመለስ ተችሏል ብለዋል፡፡
የመስክ ጉብኝቱ በወረዳው እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን በሪፖርት ከመገምገም ባሻገር በቅርበት በመከታተልና በመደጋገፍ ውጤታማ ተግባር ለማከናወን ያለመ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወረዳው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ከዲጃ ተማም ናቸው፡፡
በወረዳው ከተጎበኘ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መካከል ፍቅርና ኤደን የታሸገ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካ ይገኙበታል።ፍቅር ውሃ ፋብሪካ 3 መቶ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ በአረንጓዴ አሻራ ልማት፣በጤና፣በትምህርትና በሌሎችም የልማት ስራዎች ለማህበረሰቡ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዮስያስ ካሳ ገልፀዋል፡፡
በየጊዜው የሚገጥማቸውን የመብራት ሀይል መቆራረጥና የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
በፕሮጀክቱ በተፈጠረላቸው የስራ እድል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን የስራ እድሉ ተጠቃሚ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡
በጉብኝቱ የወረዳው አመራሮችና ባለሙያዎች የተሳተፉ በእለቱ ከተጎበኙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መካከል የውሃ ፋብሪካዎች፣የእርሻ፣የመንገድና ሌሎችም የልማት ስራዎች ይገኙበታል፡፡
ዘጋቢ ፡ በጅላሉ ፈድሉ - ከወልቂጤ ጣቢያችን