ሆርቲካልቸርን ለማስተዋወቅ ያለመ ኮንፍረንስ ሊካሄድ ነው 

የሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማስተዋወቅ ያለመ አለም አቀፍ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው፡፡

በኮንፍረንሱ ከ25 ሀገራት የተወጣጡ የዘርፉ ተዋንያንና ባለ ድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ በቅርቡ ከተዋወቁ የልማት መስኮች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ዘርፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለበርካቶች የስራ እድል በመፍጠር ለሀገሪቱም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያመጣ ነው፡፡

በ1 ሺህ 650 ሄክታር መሬት በተተከለ የሆርቲካልቸር ምርት ለ100 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር በየአመቱ ከ300 ሚሊየን ዶላር የዘለለ የውጭ ምንዛሪ ለሃገሪቱ እያመጣ መሆኑ ታውቋል፡፡

ዘርፉን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ያለመ አለም አቀፍ ኮንፍረንስ በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ላይ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

ፕሮግራሙን ያዘጋጁት የግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማህበር በመተባበር ነው፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚኒስቲር ዲኤታ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ እና የማህበሩ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ጉዳዩን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

መድረኩ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከምርምር ማዕከላት ጋር ዘርፉን ለማሳደግ ቅርርብ ለመፍጠር አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

በመድረኩ ከ25 ሀገራት የተወጣጡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ

 

 

Subcategories

የቅጂ መብት © 2019 ደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት