“ጥሩ ልምድ ተገኝቶበታል”
በገነት ደጉ
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሀገራችንና በክልላችን በተለያዩ ቦታዎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት አርሶ አደሮችን፣ ወጣቶችንና ባለሀብቶችን በማስተባበር ሰፋፊ የበጋ የመስኖ ስንዴ ሠርቶ ማሳያዎችን በማካሄድ እንዲሁም ቴክኖሎጂውን የማስተዋወቅና የማስፋት ሥራ በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
አቶ አላሮ አሻሞ የሶሮ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ በዞኑ ስንዴ በማምረት ከሚታወቁ ወረዳዎች መካከል ሶሮ አንዱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በወረዳው በደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላማ አካባቢዎች ስንዴን በስፋት በማምረት ምርታማነትን ለማሳደግ በየዓመቱ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግም አስታውሰዋል፡፡
ወረዳው በዓመታዊ ሰብሎች በመኸር ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ የሚለማ ማሳ አለው፡፡ ከዚህም ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶ በሜካናይዜሽን እና በክላስተር አሰራር የሚለሙ የሰብል ዓይነቶች ተለይተው እየተሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡
ይህንንም በመደበኛው፣ በክላስተርና በኩታ ገጠም ማሳ እንዲሁም የግብዓት አጠቃቀም በማሳደግ የስንዴ ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ አርሶ አደሩ ወትሮ የለመደው በልግን መጠበቅ ነበር፡፡ አሁን ግን ካለፈው ዓመት ተሞክሮ በመነሳት ወደ በጋ መስኖ ስራ ነው የተገባው፡፡
በወረዳው በየዓመቱ በአትክልትና ፍራፍሬ የተጀመረው ስራ አሁን ላይ ወደ በጋ መስኖ በስፋት መገባቱንም አክለዋል። በዚህም 3 ሺህ 980 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ በሆሊቲ ካልቸር ወደ 3 ሺህ 750 ሄክተር ማልማት ተችሏል፡፡
ከእቅድ አንፃርም 95 በመቶ ማሳካት መቻሉን ያነሱት አቶ አላሮ፣ በበጋ ስንዴ 7 ሺህ 797 ኩንታል ለማምረት ታቅዶ አሁን ምርት በማሰባሰብ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ ምርቱ ተጠቃሎ ባይገባም መኸር ላይ ከሚመረተው ያልተናነሰ በመሆኑ ተስፋ የሚጣልበት ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው በወረዳው ስላለው ስለበጋ መስኖ ስንዴ ማብራሪያቸውን ይቀጥላሉ፡- “በሀገር ደረጃም እንደ ከፍተኛ ልምድ ተወስዶበት በተለይም ከዚህ በፊት ያልተሞከሩ ከ2014 የምርት ዘመን ጀምሮ የተጀማመሩ ስራዎች አሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ቀበሌ ከ25 ሄክታር በላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ተዘርቶ የተሻለ ልምድና ውጤት ተገኝቷል፡፡ ይህንን ልምድ በመጠቀም የውሃ አማራጮችን በማስፋት በዘንድሮ ዓመት በሰፊው ለማምረት በ10 ቀበሌያት ተዘርቶ ጥሩ የሚባልበት ደረጃ ላይ ነው፡፡
“በአርሶ አደር፣ በወጣትና በባለሀብቱ 173 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ፣ ለዚህም ወንዝ የመጥለፍ ስራዎች በመሰራታቸው በአርሶ አደሩ ዘንድ ጥሩ ተነሳሽነትን ፈጥሯል፡፡ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 173 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ 115 ሄክታር መልማት ተችሏል፡፡ ይህም እንደ ጅምር ጥሩ ውጤት ሲሆን ሰፊ የውሃ አማራጮች ቢኖሩ ከዚያም በላይ ማልማት ይቻል ነበር ብለዋል፡፡
“እቅዱ ሲታቀድ የተጀማመሩ የፕሮጀክት ስራዎች ይጠናቀቃሉ በሚል ታሳቢ ተደርጎ ሲሆን እቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ያልተቻለው የግንባታ ስራው በተቀመጠለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ምክንያት የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረስ ባለመቻሉ ነው፡፡
“ዘንድሮ በተወሰዱ ልምዶች በተለይም ከአርሶ አደሩ ፍላጎት አንፃር ጥሩ ነገሮች በመኖራቸው ለቀጣይም ተስፋ
ሰጪ ዕድሎች አሉ፡፡ እንደ ወረዳ አርሶ አደሩን ባነቃነው ልክ ከአምና በተሻለ ልምድ የተወሰደ በመሆኑ እነዚህን አማራጮች በማስፋት በየዓመቱ የተሻሉ ስራዎችን በመስራት ውጤታማ ማድረግ ይቻላል፡፡ አርሶ አደሩም ከወትሮ በተለየ የማንንም ድጋፍ ሳይፈልግ በዘመናዊ መንገድ እና ወንዞችን በመጥለፍ ምርታማነትን እያሳደገ ነው፡፡”
ኃላፊው ጨምረው እንደገለጹት በወረዳው በተያዘው ዓመት ተጠቃሎ ሲገባ የተሻለ ምርት ሊመዘገብ ይችላል፡፡ እንደ ሀገር ስንዴ በብዛት በማምረት ወደ ውጪ ኤክስፖርት ለማድረግ ጥሩ መነሻ የሚሆን ምርታማነት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡
“እንደ አካባቢያችን የበጋ መስኖ ስንዴ ማምረት ጀምረናል፡፡ ይህም ይበል የሚያስብልና ከምግብ ዋስትና በዘለለ ኤክስፖርት ለማድረግ ተስፋ ሰጪ ነው” በማለት ሃሳባቸውን አጠናክረዋል፡፡
የበጋው መስኖ እንደተጨማሪ የሚታይ መሆኑን ያነሱት አቶ አላሮ የምርት ችግር ስለሌለ ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ ፈጠሮ በበቂ ደረጃ ማምረት እንደሚቻልና ኤክስፖርት ለማድረግ ምንም ነገር እንደማያግድ ነው የተናገሩት፡፡
ይህንንም ለማሳካት ከግንዛቤ ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶች፣ ምርታማነትን ከማሳደግ አንፃር የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የአርሶ አደሩ የኤክስቴንሽን ተግባር እና ማስልጠኛ ማዕከላት በቂ ክህሎትን እንዲሰጡ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች አምና ላይ የነበረውን ተሞክሮ በግንባር ቀደም አርሶ አደሮችና በአመራር ደረጃ ያለውን ልምድ እንዲቀስሙ መደረጉን ኃላፊው ገልፀው፣ በአንድ ቀበሌ የነበረውን ልምድ ዘንድሮ በአስር ቀበሌያት ላይ በመተግበር በ115 ሄክታር ማሳ እንዲሸፈን መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡
አጠቃላይ በወረዳው 26 የገጠር ቀበሌያት ሲኖሩ፣ በአንድ ቀበሌ አውሾና አንቆታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ብቻ በክልሉ ውሃ ስራዎች ድርጅት በተገነባው የመስኖ ግንባታ ወደ 170 ሄክታር በአትክልትና ፍርፍሬን ጨምሮ በሌሎች ሰብሎች የሚሸፈን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ቤተሰቡን ይዞ ሁለትና ከዚያ በላይ ሄክታር ስንዴ ማምረት እንዲችል እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ በዚህም የአርሶ አደሩ ፍላጎት በዘንድሮ ዓመት መጨመሩ ልምድ የተወሰደበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በወረዳው ከሜካናይዜሽን ጋር ተያይዞ ትላልቅ መስኖዎች አለመኖራቸው እንደ ችግር ታይቷል፡፡ ትላልቅ የመስኖ አውታሮች የማምረት አቅማቸው ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ ሊያለሙ የሚችሉ በመሆናቸው ወደዚያ ደረጃ ለመንደርደር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ሌላ በወረዳው አነስተኛ የመስኖ ተቋማት በሁለት ቀበሌያት ብቻ በመኖራቸው እነዚህም ከ250 ሄክታር በላይ ማልማት የማይችሉ በመሆኑ ለስራው ማነቆ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በቀጣይ ቀሪ 16ቱ ቀበሌያት ውሃ በስፋት ሊያገኙ የሚችሉትን ለመለየትና የመስኖ ግንባታውን ለማስጀመር፣ ምን
ያህል ተጨማሪ ምርት ያስፈልጋል በሚሉ ጉዳዮች ከልማት ሰራተኞችና ከአርሶ አደሩ ጋር የጋራ ውይይት ማድረግ እንደሚፈልግም አስረድተዋል፡፡
በተለይ የአርሶ አደሩ ፍላጎት ከወትሮ በመጨመሩ ብዙም የሚያስቸግር ባለመሆኑ ሁሉም አርሶ አደር የዘንድሮውን ምርት በማየት የመስራት ፍላጎት እንደተፈጠረበት አመልክተዋል፡፡
ዘንድሮ በስፋት በተመረተባቸው 10 ቀበሌያት እንደ ችግር የገጠመው ውሃ በመሆኑ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ችግሮችን በአግባቡ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡